Tuesday, September 29, 2015


እፍ በላት ጌታዬ


ወርቁ በላቸው
የክረምቱ ብርድ እንደዛሬው አልነበረም፡፡ ገና ሰኔ ሲያስገመግም የሰፈራችን ሰወች መሸበር ይይዛሉ፡፡ በጋራ የተከበበችውን መንደራችንን ልብና ሆዷን እንየቦረቦሩ፣ እንደ አንበሳ እያጋሱ፣ ቋጥኝና ዛፉን እያንከባለሉ የሚጋልቡ ወንዞች አሏት፡፡ ስለዚህ ሕፃናት ልጆች ያሏቸው ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ወንዝ እንዳይወርዱ ቀድመው ያስጠነቅቃሉ፡፡ አሮጊትና ሽማግሌዎችም ጨርቅ ለማጠብ ወይም ለሌላጉዳይ ወደ ወንዞቹ ከመሄድ ይቆጠባሉ፡፡ 

አዲስ አበባ እንደዛሬ ወንዞቿ ለአይን አስቀይሞ ጠረናቸው ከሩቅ ሳይገፋተር፣ የብዙዎቻችን መታጠቢያ፣ መዋኛና አልፎ ተርፎም መጠጥም ነበሩ፡፡ በተለይ የቀበና ገባሮች፣ ከላይ ጥንስስ ጀምሮ እስከ አባንጉሴ ድረስ የነበራቸው ገፅታ ልዩ ነበር፡፡ ሕዝብ እንዳሁኑ በብዛት አልሰፈረም፣ ቆሻሻም እንደተራራ አይቆለልም ነበረ፡፡
ክረምት ማለት ያኔ ሰማይ ተቀዶ ውሃ የሚንዠረዠርበት ወቅት ነበር፡፡ ብርዱ አጥንትን ዘልቆ መቅኒን ይነካል፡፡  በተለይ ደጋማ በሆኑ የአዲስ አበባ ክፍሎች፣ ደመናው መሬት ወርዶ እንደጢስ ሲትጎለጎል ማየት ብርቅ አልነበረም፡፡ ነዋሪው በዚህ ወቅት ጋቢና ደበሎውን ለብሶ እየቀፈፈው ነው ጉዳዩን የሚተኩሰው፡፡ ልጆች ደግሞ ጥሬያችንን እየቃምን ሰማዩን እንቃኛለን፡፡ ከአሁን አሁን ፀሀይ ወጣች እያልን፡፡
ከመንደራችን ፊት ለፊት ባለች ጠባብ መንገድ ላይ ሆነን ፀሀይን እንለምናታለን፣ ፀሀዬ ውጪ ውጪ ዳመና ተገልበጪ፣ ፀሀዬ ውጪ ውጨ ዳመና ለጎመኔ ለኔ ለኔ›››› እኛ የታች ሰፈር ልጆች እናቀልጠዋለን፡፡ የላይ ሰፈር ልጆች ደግሞ ከመንደራችን በስተ ምስራቅ አቅጣጫ ባለ ኮረብታ ላይ ይደረደራሉ፡፡ ቁልቁል እኛን እያዩ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መጮህ ይጀምራሉ፡፡ እንለምናታለን፣ ፀሀዬ ውጪ ውጪ ዳመና ተገልበጪ፣ ፀሀዬ መውጪ ውጨ ዳመና ለጎመኔ ለኔ ለኔ›››› አሁን ዳኛ የሌለው ውድድር ተጀመረ ማለት ነው፡፡ በቃ መንደሯ በእንድ እግሯ ትቆማለች፡፡ አንዳጋጣሚ ይሁን ወይ እኛን ሰምታ ፀሐዩዋ ትወጣለች፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ንትርክ ይጀመታል፡፡ የኛ መንደሮቹ ወጣች፣ ወጣች… ስንል የላይኛዎቹ ደግሞ መንጫጫት ይጀምራሉ፡፡ ነገሩ ምን መሰላችሁ፣ እኛ የምናስበው የኛ ድምፅ ከፍተኛ ስለሆነ ተሰማ ስንል፤ እነሱ ደግሞ የለም እኛ ኮረብታ ላይ ስለሆንን የተሰማው የኛ ነው ባይ ነበሩ፡፡ ሁላችንም ግን አንድ ነገር እርግጠኞች ነበርን፣ ፀሀይ በክረምት ትሰማለች፡፡ እኛ ሕፃናት የመንደራችን ብርድ ሲያንሰፈስፈን፣ ፀሃዬን እንማፀናታለን፡፡ እሷም ትታዘዘናለች፡፡
ያኔ የሚገርመኝ ነገር ግን የአያቴ ተማጽኖ ነበር፡፡ እንደ ጥጥ የነጣ ፀጉሯን ዳበስ ዳበስ እያረገች ከግቢው ባለ አንድ ትልቅ ቆርቆሮ በር ስር አጎዛ መሳይ ነገር ዘርግታ ትቀመጣለች፡፡ አንዳንዴ የሚደንቀኝ ጉዳይ ምንም ፀሀይ ሳይኖርም እጆቿን እንደ ባርኔጣ ግንባሯ ላይ ጋረድ አድርጋ ሰማዩን ቀና ብላ ፀሀዩዋን ትፈላልጋለች፡፡ ሰውነቷ የያዘው ሙቀት እያለቀና ብርዱ እያየለ ሲመጣ እትትተት…. እያለች አምላኳን መማፀን ትጀምራለች፡፡ እፍ በላት ጌታዬ …እፍ በላት ….. እየደጋገመች፡፡ እንግዲህ ለአያቴ ፀሀይ ማለት የእግዜር ምድጃ አይነት ነገር ናት፡፡ እግዜር ደግሞ መቆስቆሻ ይዞ የሚያነዳት ነዋ፡፡ ግን የሚገርመው እሷ እፍ በላት ጌታዬ ስትለው ደመና እንደ አመድ የወረሳትን ፀሀይ ግልጥ ያደርግና፣   ወከክ አድርጎ ያነድላታል፡፡ እሰይ ጌታዬ እሰይ …. እያለች ደግሞ ማመሰጋገን ትጀምራለች፡፡ አሁን ደግሞ የሚገርመኝ ለምን እፍ በያት እመቤቴ አለማለቷ ነው፡፡ ፀሀይን እንደ ማዕድ-ቤቷ እሳት ስትቆጥር ጌታ ወንድ ስለሆነ እዚያ ምን ያደርጋል አለማለቷ፡፡

No comments:

Post a Comment