Tuesday, September 29, 2015


እፍ በላት ጌታዬ


ወርቁ በላቸው
የክረምቱ ብርድ እንደዛሬው አልነበረም፡፡ ገና ሰኔ ሲያስገመግም የሰፈራችን ሰወች መሸበር ይይዛሉ፡፡ በጋራ የተከበበችውን መንደራችንን ልብና ሆዷን እንየቦረቦሩ፣ እንደ አንበሳ እያጋሱ፣ ቋጥኝና ዛፉን እያንከባለሉ የሚጋልቡ ወንዞች አሏት፡፡ ስለዚህ ሕፃናት ልጆች ያሏቸው ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ወንዝ እንዳይወርዱ ቀድመው ያስጠነቅቃሉ፡፡ አሮጊትና ሽማግሌዎችም ጨርቅ ለማጠብ ወይም ለሌላጉዳይ ወደ ወንዞቹ ከመሄድ ይቆጠባሉ፡፡ 

አዲስ አበባ እንደዛሬ ወንዞቿ ለአይን አስቀይሞ ጠረናቸው ከሩቅ ሳይገፋተር፣ የብዙዎቻችን መታጠቢያ፣ መዋኛና አልፎ ተርፎም መጠጥም ነበሩ፡፡ በተለይ የቀበና ገባሮች፣ ከላይ ጥንስስ ጀምሮ እስከ አባንጉሴ ድረስ የነበራቸው ገፅታ ልዩ ነበር፡፡ ሕዝብ እንዳሁኑ በብዛት አልሰፈረም፣ ቆሻሻም እንደተራራ አይቆለልም ነበረ፡፡
ክረምት ማለት ያኔ ሰማይ ተቀዶ ውሃ የሚንዠረዠርበት ወቅት ነበር፡፡ ብርዱ አጥንትን ዘልቆ መቅኒን ይነካል፡፡  በተለይ ደጋማ በሆኑ የአዲስ አበባ ክፍሎች፣ ደመናው መሬት ወርዶ እንደጢስ ሲትጎለጎል ማየት ብርቅ አልነበረም፡፡ ነዋሪው በዚህ ወቅት ጋቢና ደበሎውን ለብሶ እየቀፈፈው ነው ጉዳዩን የሚተኩሰው፡፡ ልጆች ደግሞ ጥሬያችንን እየቃምን ሰማዩን እንቃኛለን፡፡ ከአሁን አሁን ፀሀይ ወጣች እያልን፡፡
ከመንደራችን ፊት ለፊት ባለች ጠባብ መንገድ ላይ ሆነን ፀሀይን እንለምናታለን፣ ፀሀዬ ውጪ ውጪ ዳመና ተገልበጪ፣ ፀሀዬ ውጪ ውጨ ዳመና ለጎመኔ ለኔ ለኔ›››› እኛ የታች ሰፈር ልጆች እናቀልጠዋለን፡፡ የላይ ሰፈር ልጆች ደግሞ ከመንደራችን በስተ ምስራቅ አቅጣጫ ባለ ኮረብታ ላይ ይደረደራሉ፡፡ ቁልቁል እኛን እያዩ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መጮህ ይጀምራሉ፡፡ እንለምናታለን፣ ፀሀዬ ውጪ ውጪ ዳመና ተገልበጪ፣ ፀሀዬ መውጪ ውጨ ዳመና ለጎመኔ ለኔ ለኔ›››› አሁን ዳኛ የሌለው ውድድር ተጀመረ ማለት ነው፡፡ በቃ መንደሯ በእንድ እግሯ ትቆማለች፡፡ አንዳጋጣሚ ይሁን ወይ እኛን ሰምታ ፀሐዩዋ ትወጣለች፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ንትርክ ይጀመታል፡፡ የኛ መንደሮቹ ወጣች፣ ወጣች… ስንል የላይኛዎቹ ደግሞ መንጫጫት ይጀምራሉ፡፡ ነገሩ ምን መሰላችሁ፣ እኛ የምናስበው የኛ ድምፅ ከፍተኛ ስለሆነ ተሰማ ስንል፤ እነሱ ደግሞ የለም እኛ ኮረብታ ላይ ስለሆንን የተሰማው የኛ ነው ባይ ነበሩ፡፡ ሁላችንም ግን አንድ ነገር እርግጠኞች ነበርን፣ ፀሀይ በክረምት ትሰማለች፡፡ እኛ ሕፃናት የመንደራችን ብርድ ሲያንሰፈስፈን፣ ፀሃዬን እንማፀናታለን፡፡ እሷም ትታዘዘናለች፡፡
ያኔ የሚገርመኝ ነገር ግን የአያቴ ተማጽኖ ነበር፡፡ እንደ ጥጥ የነጣ ፀጉሯን ዳበስ ዳበስ እያረገች ከግቢው ባለ አንድ ትልቅ ቆርቆሮ በር ስር አጎዛ መሳይ ነገር ዘርግታ ትቀመጣለች፡፡ አንዳንዴ የሚደንቀኝ ጉዳይ ምንም ፀሀይ ሳይኖርም እጆቿን እንደ ባርኔጣ ግንባሯ ላይ ጋረድ አድርጋ ሰማዩን ቀና ብላ ፀሀዩዋን ትፈላልጋለች፡፡ ሰውነቷ የያዘው ሙቀት እያለቀና ብርዱ እያየለ ሲመጣ እትትተት…. እያለች አምላኳን መማፀን ትጀምራለች፡፡ እፍ በላት ጌታዬ …እፍ በላት ….. እየደጋገመች፡፡ እንግዲህ ለአያቴ ፀሀይ ማለት የእግዜር ምድጃ አይነት ነገር ናት፡፡ እግዜር ደግሞ መቆስቆሻ ይዞ የሚያነዳት ነዋ፡፡ ግን የሚገርመው እሷ እፍ በላት ጌታዬ ስትለው ደመና እንደ አመድ የወረሳትን ፀሀይ ግልጥ ያደርግና፣   ወከክ አድርጎ ያነድላታል፡፡ እሰይ ጌታዬ እሰይ …. እያለች ደግሞ ማመሰጋገን ትጀምራለች፡፡ አሁን ደግሞ የሚገርመኝ ለምን እፍ በያት እመቤቴ አለማለቷ ነው፡፡ ፀሀይን እንደ ማዕድ-ቤቷ እሳት ስትቆጥር ጌታ ወንድ ስለሆነ እዚያ ምን ያደርጋል አለማለቷ፡፡

Tuesday, September 15, 2015

Rhythm of seasons !


A beautiful beauty that quenches thirst of heart
Which fills sprit, with joy head to toe
A gift of gift, that no one can present
A treasure, dug only under, the yard of the creator
A pile of time
Packed in seasons
True and natural rhythm
Spiraling and whirling life’s dance
Beats of eternal drum
 Oh! Creator thy plans
Never collapse. 

Kiramt (rainy season) showers on sea and land
Wet  every soul, unlock door of the seed
All in the heart of earth starts to breed
Mountains adorn, with blanket of green
Valleys with run offs, and falls
Rivers fills to their brim, gush to sea leaves
Dance, with beats  of the drum, and charming rhythm


Oh! Creator Kiramt did duty
 Pass on a relay of beauty
And the skies turn clear, the sun shines free
Yellows  the grasses, shrubs and tree.
Plants comes to flower, a yellow army
Adey Abeba conquers hills and valley

Wereha Tsegie (flowering season) comes with promises
Assure that all sown will come to seed
All thrown becomes a yield.
Oh! Creator thy task gets old never
Always fresh always glitter.

How tiny are years before you
A priceless belonging
That you confer on master and servant
How cheap are days before you
A cherished good

But for you and to all a free grant. 

Worku Belachew Sept. 2015

Wednesday, September 2, 2015

Wednesday, August 12, 2015

Addis Abol :
የቲቪ ፕሮግራሞቻችን

ወርቁ በላቸው                                                                         
“ነገር ባይን ይገባል” ይላል ያገሬ ሰው፡፡  ለነገሩ በዐይን የገባ ነገር አይረሴነት አለው፣ ለማሳመንም ሆነ ለማመን ቅርብ ነው ለማለት ይሆናል እንጂ ነገር በጆሮም ይገባል… ለአደለው ደግሞ እንዲሁም ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የሆነው ይሁንና ጉዳዬ ስለብዙሃን መገናኛ ነውና በአይንም ይግባ በጆሮ  ለማነሳው ርዕስ ይጠቅመኛል፡፡

በምስልና ድምፅ የታጀቡ ቅንብሮችን፣ አሳምሮና አጣፍጦ እሳሎንድረስ ከተፍ የሚያደርግልንን ቴሎቭዥንን ነው የምናነሳሳው፡፡ እንደ ቴሌቭዥን ያለ ነገረኛ ብዙሃን መገናኛ አለ ብትሉኝ፤ አይዋጥልኝም፡፡ እንደው የማህበራዊ ኑሮ ጉዳይ ሆኖብኝ  አለ ብዬ ብቀበል እንኳ በሚዲያ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶች ይፈርዱብኛል ፣ይህንን ስል ግን እኛ አገር ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች አጥንተውና አስጠ ንተው የሼልፍ ሲሳይ ያደረጓቸውን አይለከትም፡፡ እነሱ አዛው አቧራቸውን እየማጉ ሰልፋቸውን ያሳምሩ፡፡
ዳርዳርታውን ትቼ ወደአይቀሬው ጉዳዬ ዘው ብል ይሻላል መሰል፡፡ ቴሌቭዥንን ከጓደኞቹ ለይቶ ሳሎን ምን አገባው ብሎ ለሚጠይቅ መልሱ ቀላል ነው፤ ታዲያ እንደ ዛሬው ቴክኖሎጂው ረቅቆ  እንደ ፎቶ ፍሬም ሁሉ የግድግዳ ሲሳይ ሳይሆን ማለቴ እንደሆነ ይያዝልኝ፡፡ ድሮማ ሳሎን መግባት  ብቻ አልነበረም፤ የሚሰራለት ሳጥንና የሚቀመጥበትም ቦታ እጅግ የከበረ ነበረ፡፡ ታዲያ ወደ ሳሎን ምን ከተተዋችን ስንመለስ እንደ እኔ እንደ እኔ የቴክኖሎጂው ርቀት፣ የቁሱ ጠቀሜታ እና ይህንን ተከትሎም የተቆረጠለት የገንዘብ ዋጋ ድምር ውጤት ይመስለኛል፡፡  ምስልና ድምፅን ካለበት ስቦ ነፍስ ነፍስ ዘርቶ “እነሆ በረከት” የሚል ሌላ ማን ሊመጣ ደሞኮ ስለ ዲሞክራሲ ወይም በቀጥታ ስለ እኩልነት ብናወራ፤ ይኼንኑ ተግባራዊ የሚያደርግ ብዙሃን መገኛ ቴሌቪዥን ብቻ ነው፣ ከሕፃን እስከ አዋቂ፤ ከምሁር እስከ ጨዋ፣ ከባተሌ እስከ ቦዘኔ… ሁሉን መረጃ፣ ተዝናኖትንና ትምህርትን የሚለግስ፡፡

እስኪ ዓይነ ሕሊና እዝነ ልቡናዎትን ከፈት አድርገው ያስቡት በዙሪያችንና በአለማችን ላይ የሚከናወኑ አበይት ጉዳዮቸን የቡና ስኒያችንን ከነማስቀመጫው እንደያዝንና  የሶፋችንን ትራስ እንደ ተደገፍን እነሆ ወሬ የሚል  እንደቴሌቭዥን ማን አለ? እስቲ መረጃ፣ተዝናኖትና ትምህርት የሚያቀርብ ብዙሃን  መገናኛ ጋዜጣና መፅሔት ብቻ ቢሆን አስቡት ምን እንደሚከሰት ያስተውሉት፤ ሌላው ቀርቶ  ይኽንን ጹሁፍ እንኳ ለማንበብ ስንት ኢነርጂ ማባከን እንደሚጠይቅ፤ በመጀመሪያ ማንበብ መቻል ይጠይቃል፣ ይቀጥልና ማንበብ መውደድ ይፈልጋል፣ ከዚያ ደግሞ የፀሀፊው የአንባቢን  አትኩሮት የመያዝ እና ሌሎች ተዛማጅ የፅሁፍ ክሂሎቶችን ይፈልጋል (የኔን ይኽንን ጽሁፍ እንኳ ስንቱ ገና ርዕሱን አይቶ በንዴት እንደወረወረው ኪራይ ቤት ይቁጠረው)፡፡  ምንአልባት ዛሬ ዛሬ ኢንተርኔት እየተስፋፋ ስለመጣ ይህንኑ ተከትለው የመጡ ቴክኖሎጂዎች በተወሰነ መልኩ ይወዳደሩት እንጂ ይደርሱበታል የሚል ግምት ግን የለኝም፡፡  በድረገፆች ላይ መረጃ ፈልጎ ለማግኘት እንዲያው በግርድፉ ቢያንስ ሁለት ጉዳዮችን መሻገር ይፈልጋል፤ አንድ ማንበብና መፃፍ፣ ሁለት ደግሞ ይኽንኑ ለማድረግ የኪቦርድን ቁልፎች መጫን፡፡

ላለፉት በርካታ አመታት ቴሌቭዥን የሰው ልጅ ላይ በጎ ጎኖቹን የማሳፈፉን ያህል በአንፃሩ ደግሞ አሉታዊ ተፅዕኖዎቹንም መጫኑም የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ተከባብሮ እንዲኖር ለማስቻል የሚረዱ ይዘት ያላቸው ስርጭቶች ለአየር እንደበቁ ሁሉ በተቃራኒው ደግሞ አንዱን ዘር የበላይ ሌላውን ደግሞ የበታች አድርጎ በማቅረብ ለሰው ልጆች እልቂት ዋነኛ ማሳለጫ እንደሆነ ለመጥቀስ በሕር ሳንሻገር እዚሁ ምስራቃዊ መካከለኛዋ አፍሪካ ሩዋንዳ በቂአችን ናት፡፡ የሃይማኖት እኩልነትን ተከብሮ ሰወች ራሳቸውን በሚፈልጉት መልኩ እንዲገልፁ  ማድረግ ማስቻሉ እንዳለ ሆኖ የሃይማኖትን ልዩነት በማጉላት አንዱ የሌላው እልቂት መንስኤ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን መፍጠሩም የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡  

ምንም እንኳ ቀጥዬ የማቀርበው ነገር የባቄላ ወፍጮ ቢሆንም- (መቼም ሞኝ ካልሆነ የጤፍን ወፍጮ አደባባይ ላይ የሚተክል የለም፣ ካደረጉም ዱቄቱን የንፋስ ሲሳይ ማድረግ ነዋ!)፡፡ ከማለት ግን አልቆጠብም (ገንዘብ እንጂ ነገር መቆጠብ ለምኔ!)፡፡ ወደ ነገሬ ልግባ፣ አንደ ቴሌቭዥን ያለ እጅግ ሃያል ብዙሃን መገናኛ ሃላፊነት በሚሰማቸው፣ በትምህርትም፣ በዕድሜም ሆነ በስራ ልምድን ያካበቱ እንዲሁም የሚዲያ ተፅዕኖን በደንብ የሚረዱ ሰወች ካልመሩት ጉዳቱ የሰደድ እሳት ያህል ነው፡፡ ነቄዎቹ አገራት ይህንን በማድረጋቸው ስንት እሳት እንዳይነሳ ተከላክለዋል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በጊዜ ከትኝታቸው ባንነው ስንት እሳት አጥፍተዋል፣ እንደ አፍሪቃ ባሉ አገራት ደግሞ ለጥ ብለን ተኝተን ስንት እሳት እየሞቅን እንዳለ አሁንም ኪራይ ቤት ይቁጠረው (መቼም አብዛኞቻችን ተከራዮች ነን ብዬ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ደግሞ ማጆሪቲ.. የባለቤቶችን መብት ሳንነካ ታዲያ!)፡፡
አሁንም ዳርዳር ማለት አላቆምኩም እንዴ? ወደ ፍሬ ነገሩ ልግባ፣ ይኼም ቢሆን ከብዙ በጥቂቱ እንጂ ሁሉንማ “ሰማይ ወረቀት ባህር ቀለም” ቢሆንም አይበቃንም እንበል ይሆን?
እስቲ በአለፉት ቀናት በቴሌቪዥን  ከአየሁት ውስጥ አንዱን ላንሳ፡፡ ይኼንን ፕሮግራም የአየሁት ከቤተሰብ ጋር ሆኜ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡  ለዚያውም አንድ አምስት ከሚሆኑ ሕፃናት ጋር፡፡ የኛ ሰው እውነቱን ሲነግሩት ልክ ልኩን ነግረው ያስታጠቁት ስለሚመስለው ምስልወድምፁን የአየሁነትን ጣቢያ ሳልጠቅስ፣ አድማጭ ተመልካች ደግሞ ጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ለማስቻል ጥረት አደርጋለሁ፡፡
አንድ ጠዋት ላይ እንደነገርኳችሁ ሰብሰብ ብለን የአንድ ቴሌቭዥን ፕሮግራሞችን እንከታተላለን፤ ታዲያ የማየውን ነገር ማመን አልቻልኩም.. በግልፅ የገባኝ ነገር ግን ሲጋራ እንዴት እንደሚጨስ፣ እንዴት በጭሱ ሰርክል ወይም ኦ እንደሚሰራ ፣ እንዴትና የት ሲጃራ እንደሚተረኮስ በሚገባ ያስተምራል፣ ለዚያውም ሕፃናት በሚወዱት (ለነገሩ ማንም ይወደዋል) የካርቱን ፊልም፡፡ ወይ እንደዚህ አይነት ይዘት ያለው ስርጭት አየር ላይ ሲውል  ሕጻናት እንዳያዩት የሚያስገነዝብ ማስጠንቀቂያ መናገር፣ አልያ ደግሞ ከነጭራሹ  አለማሳየት ሲቻል፡፡ የሲጃራን ነገር ካነሳሁ ሳልዳስሰው ማለፍ የሌለብኝ ነገርም አለ፡፡ በተለይ ፊልም ሰሪዎቻችን ማስተዋል ያለባቸው ነገር ፊልሞቻቸውን ከሚመለከቱላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ እንደው ጥናት ብጤ እንኳ ባላደርግ የግል ምልከታዬ እንደሚያስረዳኝ፣ አስራስምንት አመት ያልሞላቸው የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አብዣኛውን ቁጥር ይይዛሉ ባይ ኘኝ፡፡ ይኼንን ስል ግን ሲኒማ ገብተው ሳይሆን በእየቤታቸው ያሉትን ማለቴ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ተመልካች እያለ ሲጃራና መጠጥን በሚያማልል መልኩ እየጠጡ ያልተከፈለበት ማስታወቂያ መስራቱ ለምን አስፈለገ? ከመቼውም ግዜ በላይ እንደ እንጉዳይ እየተፈለፈሉ ባሉት የቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማዎቻችን ላይስ ይህ አይነቱ ድርጊት ቸል መባል ይኖርበት ይሆን? የዘፈን ክሊፖቻችን እና የመሳሰሉትም በዚሁ አንቀፅ ይካተቱልኝ፡፡ በተለይ አንዳንድ ቀሚሳቸው ጠልፎ ሊጥላቸው የሚደርሱ ቆነጃጅቶች ጉዳይ ደግሞ በቀይ ይሰመርልኝ፡፡   ይኼንን ጉዳይ ቀለል ባናደርገው ጥሩ ይመስለኛል፤ አለበለዚያ ሲሰድቡት ዝም ያለ ሲመቱትም ያው ነው ሆኖ ይኼንን ዝም ስንል ቀስ በቀስ የምንፀየፋቸው ነገሮች ሁሉ እየተንፏቀቁ መምጣታቸው አይቀሬ ነው ባይ ነኝ፡፡